Isaiah 18

በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ትንቢት

1በኢትዮጵያ ወንዞች ዳር ለምትገኝ፣
ፉር ፉር የሚሉ ክንፎች ላሉባት
ወይም፣ አንበጣ ማለት ነው።
ምድር ወዮላት!
2ይህችውም መልእክተኞችን በባሕር፣
ከወንዞች ማዶ በደንገል ጀልባ የምትልክ ናት።

እናንት ፈጣን መልእክተኞች
ረዣዥምና ቈዳው ወደ ለሰለሰ፣
ከቅርብም ከሩቅም ወደሚፈራ ሕዝብ፣
ኀያልና ቋንቋው ወደማይገባ፣
ወንዞች ምድሩን ወደሚከፍሉት መንግሥት፣ ሂዱ!

3እናንት የዓለም ሕዝቦች፣
በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፣
በተራሮች ላይ ምልክት ሲሰቀል ታዩታላችሁ፤
መለከትም ሲነፋ ትሰሙታላችሁ።
4 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤
“ጸጥ ብዬ እቀመጣለሁ፤
ከማደሪያዬም በፀሓይ ሐሩር እንደሚያስፈልጋችሁ ብርቅርቅ ትኵሳት፣
በመከርም ሙቀት እንደ ደመና ጠል ሆኜ እመለከታለሁ።”
5ከመከር በፊት የአበባው ወቅት ሲያልፍ፣
አበባው የጐመራ የወይን ፍሬ ሲሆን፣
የወይን ሐረጉን ተቀጥላ በመግረዣ ይገርዘዋል፤
የተንሰራፋውንም ቅርንጫፍ ቈራርጦ ያስወግደዋልና።
6ሁሉም በተራራ ላይ ለሚኖሩ ነጣቂ አሞሮች፣
ለዱርም አራዊት ይተዋሉ፤
አሞሮች በጋውን ሁሉ ሲበሉት ይባጃሉ፤
የዱር አራዊትም ክረምቱን ሁሉ ሲበሉት ይከርማሉ።
7በዚያን ጊዜ ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር
ረዣዥምና ቈዳው ከለሰለሰ፣
ከቅርብም ከሩቅም ከሚፈራ ሕዝብ፣
ኀያልና ቋንቋው ከማይገባ፣
ወንዞችም ምድሩን ከሚከፍሉት መንግሥት፣ ገጸ በረከት ይመጣለታል፤
ገጸ በረከቱም የሚመጣለት የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስም ወዳለበት ወደ ጽዮን ተራራ ነው።

Copyright information for AmhNASV